ከፍተኛ ፈጻሚ ቡድን ተደጋጋፊ ክህሎቶች ያላቸው ለጋራ ዓላማ ቁርጠኛ የሆኑ፣ ግቦችን የሚፈጽ እና እራሳቸውን በጋራ ተጠያቂ የሚያደርጉበት የጋራ አቀራረብ የሚከተሉ አነስተኛ የሰዎች ቡድን ነው፡፡
የከፍተኛ ፈጻሚ ቡድን ባህሪያት:
- የጋራ ራዕይና ዓላማ: እያንዳንዱ ሰው የኩባንያውን ተልዕኮ በጥልቀት በመረዳት ለተልዕኮው ቁርጠኛ ይሆናል፡፡ የሚሰራው ለደመወዝ ብቻ ሳይሆን በግቡ ያምንበታል፡፡
- ግልጽ የሥራ ድርሻዎችና ኃላፊነቶች: እያንዳንዱ አባል ለምን ተጠያቂ እንደሚሆን እና የሱ ስራ እንዴት ለቡድኑ ስኬት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ያውቃል፡፡ ይህ ግራ መጋባትና የስራ መደራረብን ይቀንሳል፡፡
- እምነት እና የሥነ ልቡና ደህንነት: የቡድን አባላት ተጋላጭ ሲሆኑ ደህንነት ይሰማቸዋል፣ ስህተተቶችን አምነው ይቀበላሉ እንዲሁም የፈጠራ ሀሳቦችን ያለ ወቀሳ ወይም መዋረድ ፍርሀት ያቀርባሉ፡፡ ይህ የፈጠራ መሰረት ነው፡፡
- ክፍትና ግልጽ ግንኙነት: ገንቢ የሆነ የግብረ መልስ መስጠትና መቀበል አለ፡፡ አስቸጋሪ ውይይቶች አይሸሹም፡፡ ቡድኑ በግልጽነትና በመከባበር ግንኙነት ያደርጋል፡፡
- ውጤታማ የውሳኔ አሰጣጥና የግጭት አፈታት ሂደቶች፡ ቡድኑ የግል ከማድረግ ይልቅ ውሳኔ በሚሰጥባቸው እና አለመግባባቶች ውጤታማ በሆነ መልኩ በሚፈቱባቸው መንገዶች ላይ ይስማማል፡፡
- የጋራ ተጠያቂነት: አባላት ለከፍተኛ ደረጃዎች አንዳቸው ሌላኛቸውን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡ የሆነ ስህተት ሲፈጠር ይህን መመልከት የመሪው ብቻ ስራ ሳይሆን የቡድኑ አባላት ለጋራ ውጤት ኃላፊነት ይወስዳሉ፡፡
የቡድን ምስረታ ደረጃዎች
ሁሉም ቡድኖች በተፈጥሮ ደረጃዎችን ያልፋሉ፡፡ እንደ መሪ የእርስዎ ስራ በእያንዳንዱ ደረጃ ላይ ቡድኑን መምራት ነው፡፡
- ምስረታ: ይህ ቡድኑ ለመጀመሪያ ጊዜ በጋራ የሚገናኝበት የመጀመሪያው ደረጃ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ትሁት፣ ደስተኛ እና በመጠኑ ተጠራጣሪ ነው፡፡ አባላት የስራ ድርሻቸውን ለመረዳት እና እርስ በርስ ለመተዋወቅ ይሞክራሉ፡፡
የመሪው የሥራ ድርሻ: ግልጽ መመሪያ ይሰጣል፣ ግቦች ያስቀምጣል እንዲሁም ትውውቆችን ያመቻቻል፡፡ በግልጽ የሚገኝ እና ተደራሽ ይሆናል፡፡
- ግጭት: ይህ ደረጃ ግጭትና ፉክክር የሚታይበት ነው፡፡ የቡድን አባላት ገደቦችን ለማለፍ ይሞክራሉ፡፡ የስራ ድርሻዎችን፣ የስራ ዘይቤዎችን እና የመሪውን ስልጣን በተመለከተ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች የተለመዱ ናቸው፡፡ ይህ ደረጃ ለቡድኑ ለማደግ አስፈላጊ ነው፡፡
የመሪው የሥራ ድርሻ: አለመግባባቱን ዝም ብሎ አያልፍም፡፡ ለቡድኑ እንዴት አለመግባባቶችን በአክብሮት መያዝ እንዳለበት ያስተምራል፣ የቡድኑን ዓላማ ደግሞ ይገልጻል እንዲሁም ለቡድኑ ግቦቹን ያስታውሳል፡፡ እንደ አስፈላጊነቱ አስታራቂ ይሆናል፡፡
- አሰራር ማዘጋጀት: ቡድኑ ልዩነቶቹን በመፍታት ወደ ስምምነቶች ይመጣል፡፡ እንዴት አብረው እንደሚሰሩ “አሰራሮችን” ወይም ህጎችን ያዘጋጃል፡፡ እምነትና መከባበር እያደገ ይሄዳል፡፡ የቡድን አባላት እርስ በርሳቸው መረዳዳት ይጀምራሉ፡፡
የመሪው የሥራ ድርሻ: ትንሽ ወደ ኋላ በማፈግፈግ ቡድኑ ተጨማሪ ኃላፊነት እንዲወስድ ያደርጋል፡፡ ስኬቶችን በማብሰር አዎንታዊ አሰራሮችን ያጠናክራል፡፡
- መፈጸም: ቡድኑ አሁን በአግባቡ ዘይት እንዳገኘ ማሽን በሳል፣ የተደራጀ እና በአግባቡ የሚሰራ ይሆናል፡፡ አባላቱ ግቦችን በማሳካት ላይ ያተኩራሉ፣ ችግሮችን በራሳቸው መፍታት ይችላሉ እንዲሁም በከፍተኛ ደረጃ ውጤታማ ይሆናሉ፡፡
የመሪው የሥራ ድርሻ: ተጨማሪ ስራዎችን ይመድባል እንዲሁም እያንዳንዱን የቡድን አባል አቅም በማሳደግ ላይ ያተኩራል፡፡ ቡድኑን ለማነሳሳት አዳዲስ ፈተናዎችን ይመለከታል፡፡
ምሳሌ: ዮሀንስ የንጹህ ማብሰያ ቡድኑን ይመሰርታል
ዮሀንስ ጓደኛውን (የመገጣጠም መሪ) እና የአክስት/አጎቱን ልጅ (የሽያጭ አስተባባሪ) አድርጎ ይቀጥራል፡፡
መመስረት:-በመጀመሪያው ቀን ዮሀንስ ስብሰባ በመጥራት የንግድ ስራውን ራዕይ ይገልጻል፡፡ ሁሉም አባላት ደስተኛና ትሁት ናቸው፡፡ ለአባላቱ ግልጽ የመጀመሪያ ስራዎች ይሰጣቸዋል፡፡
ግጭት: ከሁለት ሳምንት በኋላ ጓደኛው እና የአክስት/አጎቱን ልጅ አለመግባባት ውስጥ ይገባሉ፡፡ የሽያጭ አስተባባሪው ለደንበኛ የማስረከቢያ ቀን ቃል የገባ ሲሆን የመገጣጠም መሪው ይህን ቀን ማሟላት እንደማይቻል ይናገራል፡፡ በዚህ የተነሳ በዮሀንስ ፊት ይከራከራሉ፡፡ ዮሀንስ ለአንድ ወገን ከመወገን ይልቅ ሁለቱን አንድ ላይ ያገናኝ እና “አሰራር እናዘጋጅ፣ የሽያጭ አስተባባሪው ለየትኛውም ቀን ቃል ከመግባቱ በፊት ለመገጣጠም መሪው ማሳወቅ አለበት፡፡” ብሎ ይነግራቸዋል፡፡
አሰራር: ቡድኑ በዚህ ህግ ላይ ይስማማል፡፡ ምርትና ሽያጭን ለማቀናጀት ሳምንታዊ ስብሰባ ማካሄድ ይጀምራሉ፡፡ የበለጠ እርስ በርስ መተማመን ይጀምራሉ፡፡
መፈጸም: ከሁለት ወራት በኋላ ቡድኑ ስራውን በተሳለጠ ሁኔታ ይሰራል፡፡ የመገጣጠም መሪው በየሳምንቱ ምን ያክል ምድጃዎች ዝግጁ እንደተደረጉ ለሽያጭ አስተባባሪው በንቃት ይነግረዋል፡፡ ሁለቱ የዮሀንስን ጣልቃ መግባት ሳይፈልጉ የአቅርቦት ችግርን ለመፍታት በጋራ ይሰራሉ፡፡